Amharic Bible

ትንቢተ ሕዝቅኤል
Chapter 1 of 48
left-arrow Chapter - 1 right-arrow
Verse 1

በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፥ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ።

Verse 2

ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት

Verse 3

ከወሩም በአምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በከለዳውያን አገር በኮቦር ወንዝ ወደ ቡዝ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፥

Verse 4

እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም እሳት መጣ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፥ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ እንደሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ ነበረ።

Verse 5

ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር።

Verse 6

ለእያዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት።

Verse 7

እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፤ የእግራቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፤ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር።

Verse 8

በክንፎቻቸውም በታች በእያራቱ ጐድናቸው እንደ ሰው እጅ ነበረ፤ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው።

Verse 9

ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ የተያያዘ ነበረ፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር፥ እያንዳንዱም ፊቱን አቅንቶ ይሄድ ነበር።

Verse 10

የፊታቸው አምሳያ እንደ ሰው ፊት ነበረ፥ ለአራቱም በስተ ቀኛቸው እንደ አንበሳ ፊት፥ በስተ ግራቸውም እንደ ላም ፊት ነበራቸው፥ ለአራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው።

Verse 11

ክንፋቸውም በላይ ተዘርግቶ ነበር፥ የእያንዳንዱም ሁለት ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፥ ሁለት ሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር።

Verse 12

እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።

Verse 13

በእንስሶቹ መካከል እንደሚነድድ የእሳት ፍም ያለ ምስያ ነበረ፤ በእንስሶች መካከል ወዲህና ወዲያ የሚሄድ እንደ ፋና ያለ ምስያ ነበረ፤ ለእሳቱም ፀዳል ነበረው፥ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር።

Verse 14

እንስሶቹም እንደ መብረቅ ምስያ ይሮጡና ይመለሱ ነበር።

Verse 15

እንስሶችንም ስመለከት፥ እነሆ፥ በአራቱ እንስሶች አጠገብ በምድር ላይ አንድ አንድ መንኰራኵር አየሁ።

Verse 16

የመንኰራኵሩም መልክ እንደ ቢረሌ ነበረ፤ አራቱም አንድ አምሳያ ነበሩ፤ ሥራቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ።

Verse 17

በእያራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።

Verse 18

ቁመታቸውም የረዘመና የሚያስፈራ ነበረ፤ የአራቱም ክበብ ዙሪያው በዓይን ተሞልቶ ነበር።

Verse 19

እንስሶቹም በሄዱ ጊዜ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ሄዱ። እንስሶቹም ከምድር ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ መንኰራኵሮቹ ከፍ ከፍ አሉ።

Verse 20

መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱ ሄዱ፤ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና መንኰራኵሮቹ በእነርሱ አጠገብ ከፍ ከፍ አሉ።

Verse 21

የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና እነዚያ ሲሄዱ እነዚህ ይሄዱ ነበር፤ እነዚያም ሲቆሙ እነዚህ ይቆሙ ነበር፤ እነዚያም ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር።

Verse 22

ከእንስሶች ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር።

Verse 23

ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት።

Verse 24

ሲሄዱም የክንፎቻቸው ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ፥ እንደ ሁሉን የሚችል የአምላክም ድምፅ፥ እንደ ታላቅም ሠራዊት ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

Verse 25

በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

Verse 26

በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ።

Verse 27

ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ።

Verse 28

በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።

Chapter -
1